Wednesday 10 August 2016

ታሪካዊ የለውጥ ጎዳና ለኢትዮጵያ

ኢትዮጵያዊያን እጅግ የተቀናጀ ያመረረና ቀጣይነትም ያለው የሚመስል ተቃውሞ በመንግስት ላይ እያካሄዱ ይገኛሉ። ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሏል። የአዲስ አበባ የመስፋፋት እቅድና የመሬት ቅርምት እና የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ቢያነሳሱትም መሠረታዊ የሆኑ የመብትና የነጻነት እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ትግሉ በሰላማዊ ሰልፍ ተጀምሮ ሁለ ገብ የሆኑ ስልቶችን ወደ መጠቀም የተሸጋገረ ይመስላል። በመቶዎች የሚቆጠሩት ሰልፈኞች በመንግስት ታጣቂዎች ተገለዋል ቆስለዋል ታስረዋል። ከመንግስት በኩልም ቁጥራቸው ያልታወቀ ወገኖች ሞተዋል ቆስለዋል።  የታሰሩ ግን የሉም። ይህም ሁሉ መከራ ወርዶ ህዝቡ ለበለጠ ትግል ተነሳስቷል። እስካሁን የተከናወኑት ክስተቶች እንዲሁም ህዝቡ የሚያስተጋባቸው መፈክሮች በግልጽ እንደሚያሳዩት መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ በህዝቡ ዘንድ  ተቀባይነትን እንዳጣ ለመረዳት ችሏል። ለመሆኑ ህዝባዊ ትግሉ አስፈላጊ ነውን?  

የትግሉ አስፈላጊነት

ለእኔ ትግሉ የዘገየ ቢሆንም እጅግ አስፈላጊ ነው! ምክንያቶችም ግልጽ ናቸው።
  • በሁሉም የመንግስት መዋቅሮች ያሉት ሓላፊዎች ከአንድ አካባቢ የመጡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አምባ ገነኖች ዘረኞች፣ ሙሰኞች፣ ገዳዮችና አፋኞች ናቸው 
  • የሲቪክና የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ በሙሉ በገዥው ቡድን ተይዘዋል ህዝብን አሳዳጅ እንዲሆኑ ተደርጓል 
  • ኢኮኖሚው በኤፈርትና በሜድሮክ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ወድቋል ንጹሐን ባለሀብቶች በዘዴ ከጫወታ ውጭ ተደርገዋል 
  • ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የሚቆርሱት ዳቦ አጥተዋል
  • ኢትዮጵያዊያውያን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ለስደት ተዳርገዋል በውጭ አገራት መከራ ሲገጥማቸው መንግስት ጀሮ ዳባ ልበስ ብሏል
  • ስለመብት መጣስ የተናገሩ ፍጹም ሰላማዊ ሰዎች ተገለዋል ታስረዋል አካለ ስንኩላን ሆነዋል ተሰደዋል ቤተሰቦቻቸውም በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል
  • የኢትዮጵያ ታሪክና ድንበር በማናለብኝነት ተንቋሿል ተቆርሷል 
  • ኢትዮጵያዊያን በዘራቸው እንዲከፋፈሉ በጥርጣሬ እንዲተያዩ በዘመቻ ተሠርቷል 
  • ትምህርትን በማስፋፋት ስም ትውልዱ ታፍኗል ተምሮ ያልተማረ ሆኗል የትምህርት ክብርና ጥቅም ወድቋል 
  • በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራችን በሁሉም የሥልጣኔ መለኪያዎች የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች 
  • እውነትን የሚያሳውቁ የመገናኛ ብዙኅን ተዘግተዋል ሠራተኞቻቸው ታስረዋል ተሰደዋል 
  • ባጠቃላይ ሲታይ ራሱ ያወጣውን ሕገ መንግስት እንኳ ማክበር ያልቻለ መንግስት ነው 

የትግሉ ዓላማና መርሆች

መንግስት እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ 25 ዓመታት ያህል ተጠብቋል። ሆኖም ችግሮች እየተባባሱ እንጂ እየቀነሱ አልሄዱም። ከዚህ በላይ መንግስት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠው ዘንድ አግባብ እንዳልሆነ ህዝቡ እየተናገረ ነው። እንዲህ ከሆነ በመካሄድ ላይ ያለው የህዝብ ትግል ዓላማው ምን መሆን ይኖርበታል? የህዝቡ ጥያቄ ከወልቃይትና ከመሬት ቅርምት ጋር ከተያያዙ ጥያቄዎች ያለፈ ነው። ውድ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት የሆኑለት ዓላማ የላቀ  ነው። 


አጠቃላይ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ታይቷል። ጥያቄው መሠረታዊ ለውጥ ሲባል ምን ማለት ነው የሚል ነው። ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ መስጠት ትግሉ ውጤታማ እንዲሆንና አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይኖር ያደርጋል።    


ከላይ ከተዘረዘሩት የትግሉን አስፈላጊነት ከሚያጎሉት ምክንያቶች እንዲሁም ህዝቡ እያስተጋባው ካለው መፈክር በመነሳት ትግሉ መቆም ያለበት ፍጹም ዘለቄታ ያለው ፍትህና ነጻነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።  ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም መሸማቀቅ አስበው ተናግረው ሠርተው የሚኖሩባት የሚኮሩባት አገር ይናፍቃሉ። ማንኛውም ዜጋና የመንግስት አካል እኩል ከሕግ በታች የሚሆንባት አገር ትመሰረታለች።  ይህን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ግን ትግሉ በመርሆች ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል ቀጥለው የተዘረዘሩትን መርሆችና የአቋም መግለጫዎች ግምት ውስጥ ያስገባ ትግል በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተጠናክሮ  ይቀጥል ዘንድ ያስፈልጋል።
  • ኢትዮጵያዊያንን ለማሸማቀቅና ለማፈን የወጡ ሕጎች ተቀባይነት የላቸውም 
  • የትግሉ ዓላማ ለኢትዮጵያዊያን ዘላቂ ፍትህና ነጻነት ለማምጣት እንጅ የመንግስት ባለሥልጣንንና አጋሮቻቸውን ለማሳደድ አይደለም  
  • የመንግስት ባለሥልጣንንና አጋሮቻቸው የለውጡ አካል መሆን አለባቸው 
  • ትግሉ የህዝብ ስለሆነ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመራ አይችልም። ይልቁንስ ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍል የወከለ ታማኝና አስተዋይ ግለሰቦችን ያካተተ ልዩ ብሄራዊ ግብረ ሓይል ይመሰረታል  
  • በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የትግሉ አካል መሆን አለበት
  • በትግሉ ወቅት የመንግስትም ሆነ የመንግስት ደጋፊ ግለሰብ ንብረት አይወድምም። ይልቁንስ ለትግሉ መፋፋም ሊያግዝ ይችላል  
  • ትግሉን ለማኮላሸት የሚጥሩ ካሉ በምክር እንዲመለሱ ይደረጋል። ይህም ካልሆነ ከማንኛውም የማኅበረሰብ ሱታፌዎች ይገለላሉ 
  • የሃይማኖት ተቋማት በአንድም በሌላም መንገድ ትግሉን ከማቀዝቀዝ መታቀብ አለባቸው 
  • ትግሉ ፍጹም ሰላማዊ ነው። ዳሩ ግን የመንግስት ታጣቂዎች እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ማናቸውም አዋጭ የትግል ስልቶች ሥራ ላይ መዋል ይችላሉ  
  •  ህዝባዊ ትግሉን ለሚያስተባብሩ ወገኖች ህዝቡ የደኀንነት ጥበቃ ያደርጋል 
  • በትግሉ ወቅት የወደቁና የሚወድቁ ውድ ኢትዮጵያዊያን የሰማዕትነት ክብር ይሰጣቸዋል 
  • ትግሉ የኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን በመሆኑ የምዕራብ አገሮች ላይ ጥገኛ አይሆንም

ባለድርሻ አካላት

ከላይ የተዘረዘሩትን ዓላማዎች በተሳካ ሁኔታ ለመምታት የተለያዩ አካላት ልዩ ሱታፌ ማድረግ አለባቸው በታሪካችን ከዚህ በፊት የተካሄዱት የለውጥ ሙከራዎች ዘለቄታዊነት ያለው ውጤት ያላመጡት በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ቢሆንም ዋናው ግን ባለድርሻ አካላት እንደሚገባቸው ባለመሥራታቸው ነው የለውጡ መሪ አንድ ፓርቲ ወይም ወታደሩ ስለነበር የፈለግነውን ውጤት አላገኘንም ከዚህ ተመሳሳይ አዙሪት ለመዳንና ኢትዮጵያዊያን ወደማያዳግም ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲሸጋገሩ ከተፈለገ ትግሉ ሁሉን አሳታፊና አቃፊ መሆን ያስፈልገዋል   

በመሆኑም መንግስትና ደጋፊዎቹ ትግሉን በማካሄድ ላይ ያለው ሰፊው ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃይማኖት ተቋማትና የመገናኛ ብዙኅን ልዩና ላቅ ያለ አስተዋጽዖ ማድረግ ያስፈልጋል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከልምዳቸው በመነሳት ለትግሉ የሚጠቅሙ ስልቶችንና ግብአቶችን ሊያቀርቡ ይችላሉ ዳሩ ግን ትግሉን ለሥልጣን ሲሉ ብቻ ለመቆጣጠር የሚሞክሩ እንዳይኖሩ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሃይማኖት ተቋማት ለእውነት መቆምና አማኞቻቸውም መንግስትን የመቃወም መብት እንዳላቸው መቀበል አለባቸው ኢትዮጵያም በውጭውም ዓለማት ያሉ የመገናኛ ብዙኅንም እየሆነ ያለውን እውነታ በወቅቱ መዘገብ እንዲሁም ህዝብን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ዝግጅቶችን ከማቅረብ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል እንዲያውም አንድነትን ፍትህንና ነጻነትን የሚሰብኩ ሥራዎችን ማቅረብ አለባቸው ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የመንግስትና የደጋፊዎቹ ድርሻንና አስፈላጊነት ሰፋ አድርጌ ለማሳየት ልሞክር            


መንግስትና ደጋፊዎቹ

ምንም እንኳን በሕግ እንደሚታወቀው መንግስትና ገዥ ፓርቲ የተለያዩ ቢሆኑም በነባራዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሁለቱ አንድ ናቸው ኢሕአዴግ ፓርቲም መንግስትም ነው ኢሕአዴግ የሆነ ሁሉ ግን እኩል መብትና አቅም የለውም ሕወሐት የመንግስት መሥራች አስኳልና አጥርም ነው ሌሎች ኦሮሞውን አማራውንና ደቡቡን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች የሕወሐት ተባባሪዎች ናቸው ቢባል አይጋነንም የሆነው ሆኖ መንግስት የለውጡ አካል መሆን አለበት ስል ሕወሐትን ብአዴንንም ኦሕዴድንም እንዲሁም ደሕዴድንም ይመለከታል ይህ መንግስት የሚቆጣጠራቸውን የስለላ ተቋሙን  ወታደሩን ፖሊሱንና ሚሊሻውንም ይመለከታል የመንግስት ደጋፊዎች ስል ደግሞ በቢዝነስም ይሁን በርዕዮተ ዓለም መንግስትን የሚደግፉና ከሱም ጋር በሽርክና የሚሠሩትን ኢትዮጵያ ውስጥና በውጭው ዓለም ያሉትን ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ያካትታል

ከዚህ በፊት የተካሄዱት አብዮቶች በጥሎ ማለፍና በጥቃትና በበቀል ላይ የተመሰረቱ ናቸው ደርግ የጃንሆይን መንግስት የለውጡ አካል ለማድረግ ጥቂት ሞከረና ወደ እብሪት ተሸጋገረ በደመ ነፍስ ንጹሐን ኢትዮጵያዊያንን ሳይቀር በጅምላ ረሸነ የደርግን ጥሩነት ለማሳየት የጃንሆይ የነበሩትን ሁሉንም ሥራዎች ማውገዝን ተያያዘው በዚያም የተነሳ ቀላል የማይባል የህዝብ ድጋፍ አጣ አይወድቁ አወዳደቅ ወደቀ ያሁኑ መንግስትም 25 ዓመት ሙሉ ደርግን በማውገዝ የራሱን ንጽህናና ልማታዊነት ለማሳየት ይጥራል ከዚያም አልፎ ስህተቱን የሚነግሩትን ወገኖች ነፍጠኛና ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ በማለት ያሸማቅቃል ባጠቃላይ በዚህ መንግስት ዐይን ሲታይ የደርግ የነበረው ሁሉና  ስለኢትዮጵያ የሚናገር የተወገዘ ነው የደርግ ደጋፊዎች የነበሩም እንደ ዜጋ አይቆጠሩም ይህ አስተሳሰብ ግን ለመንግስት ኪሳራ እንጅ ትርፍ አላስገኘለትም    

      
ያሁኑ ህዝባዊ ትግል ግን ፍጹም የተለየ መሆን አለበት ዘላቂ ሰላም እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት ለማምጣት ሰላም እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት እንዳይኖር የጣረውና የሚጥረው መንግስትና ደጋፊዎቹም መካተት አለባቸው ይህም የታሰበው ስለአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው አንደኛ በመንግስት መዋቅርና በሽርክና የሚሠሩ በሀሳብና በሞራልም የሚደግፉ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ እነሱም የለውጡ አካል ቢሆኑ ትግሉ ዓላማውን በቶሎ ያሳካል ሁለተኛ መንግስትና ደጋፊዎቹም ቢሆኑ እውነተኛ ነጻነት ፈላጊዎች ሊሆኑ ይችላሉሦስተኛ በብድርና በእርዳታ እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀውን መንግስትን የለውጡ አካል ማድረግ የይቅርታና የርህራሄ መንፈስን ስለሚያንጸባርቅ ትግሉ ሰላማዊ ይሆናል አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነትንና የንብረት ውድመትን ያስቀራል አራተኛ መንግስትንና ደጋፊዎችን የለውጡ አካል ማድረግ ለነገው ትውልድ የማይረሳ ትምህርትን ይሰጣል ለውጥ የሚመጣው በማጥቃትና በማግለል ሳይሆን በዳይንም ተበዳይንም በማሳተፍ እንደሆነ ትውልዱ ይረዳል እንደ ባህልም ይይዘዋል         

ዳሩ ግን መንግስትና ደጋፊዎቹ የለወጡ አካል ሊሆኑ የሚችሉት ለሥልጣን ከመስገብገብና ከስሜት ወጥተው ለምስኪኑ ዜጋ ማሰብ ሲጀምሩ ነው የተገነቡ ሕንፃዎችንና መንገዶችን እንዲሁም የተመሰረቱ ብሄር ተኮር ፓርቲዎችን ብቻ እያነሳሱ መመፃደቅ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ይኖርበታል ኢትዮጵያ ያለባትን የገንዘብ እዳ የህዝቡን ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ሕይወት የእስር ቤቶችንና  የታሳሪዎችን ብዛት የተሰደዱትንና በሂደቱም የሞቱትን ወዘተ በማስታወስ የማዘንና የመጸጸት ከዚያም ለውጥ ለማምጣት የማመን አዝማሚያ መታየት አለበት ጊዜው የፈለጉትን ገሎና ዘርፎ ውጭ አገር በሰላም መኖር የሚቻልበት እንዳልሆነ ማሰብም ይጠቅማል መንግስትና ደጋፊዎቹ በዚህ ወሳኝ የለውጥ ሂደት ቢሳተፉ ታሪክና ልጆቻቸው በበጎ እንደሚያነሷቸው እስካሁንም ለተሠሩ ስህተቶችና ግፎች ማርከሻ ወይም ንስሃ እንደሚሆን ማወቅ አለባቸው ዛሬና ነገ እውነተኛና ዘላቂ ለውጥ ለማድረግ ያሰበን አካል ህዝቡ በትናንት በደሉ ሊፈልገው አይችልምና! ስለዚህ ባለቀ ሰዓት መንግስት የማይረሳ እንቁ ታሪክ የመሥራት እድሉ አለው      

መንግስት ተሳትፎውን በልዩ  ልዩ  መንገዶች  መግለጽ መጀመር ይችላል። ለውጡን የሚያስተባብር ልዩ ብሄራዊ ግብረ ኃይል ቶሎ እንዲቋቋም መፍቀድ በሱም መሳተፍ ለሰልፍ የሚወጡት ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰድ ለችግሮችም መፍትሔ እንደሚሰጥ ማሳወቅ በትግሉ ምክንያት የታሰሩትን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት የመንግስት መገናኛ ብዙኅን ከአጉል ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲታቀቡ ማድረግ ባጠቃላይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሕግ ከለላ ማድረግ ወዘተ ሊሆን ይችላል።     

ልዩ ብሄራዊ ግብረ ኃይል

ከላይ እንደተገለጸው አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ለውጥ ለማምጣት መንግስት አቅምም ፍላጎትም እንዳለው ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ አላሳየም። አሁን ተነስቶ ይህን ለማድረግ ቃል ቢገባ እንኳን ማንም አይቀበለውም። መንግስት ከኦርቶዶክሱ ከሙስሊሙ ከአማራው ከኦሮሞው ከጋምቤላው ከአፋሩ ከሶማሌው ከጉራጌው ወዘተ በደንብ ተለያይቷል። በአንጻሩም ይህን ትግል በተሳካ ሁኔታ ሊመራ የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ላለፉት በርካታ ዓመታት በዘመቻ ተሠርቷል። ትግሉን ህዝቡ እንደጀመረ ህዝቡ ይጨርስ ማለት ደግሞ አይቻልም። በየዕለቱ 100 ሚሊዮን ህዝብ ሰልፍ መውጣት የለበትም። ህዝቡ የትግሉ ባለቤትና ኦዲተር ሆኖ አሥፈጻሚ አካል ወይም ልዩ ብሄራዊ ኮሚቲ ያስፈልገዋል። ይህን ልዩ አካል መምረጥ ያለበት ህዝቡ ራሱ ነው። 


ኮሚቴው ለምንና እንዴት መመረጥ እንዳለበት ለመነሻ ያህል ጥቂት ነጥቦችን ላንሳ።         
  • የዚህ አካል ዋና ዓላማ ፍጹም ግለሰባዊና ቡድናዊ ነጻነት ፍትህና ዴሞክራሲ የሚገዛው መንግስት ለመመስረት የሚያስችሉ ጉዳዮችን መለየትና ተግባራዊ ማድረግ ነው   
  • ሥራውንም ለዚሁ ተብሎ በሚዘጋጀው መንገድ ለህዝብ በየጊዜው ያሳውቃል  
  •  ዝርዝር የሥራውን ጠባይና አይነት ከባለቤቱ ከህዝቡ ያገኛል
  • አሥፈጻሚው አካል ወይም ልዩ ኮሚቴው በብሄራዊ ደረጃ መዋቀር አለበት። ከመንግስትና ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦች መካተት ይኖርባቸዋል። ዳሩ ግን በዘር ላይ የተመሰረተ ውክልና እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል 
  • የሚመረጡት ግለሰቦች ከሙስና ከዘረኝነትና ከድንቁርናና ነጻ የሆኑና የሥልጣን ጥም  ያላገኛቸው ለእድገትና ለለውጥ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያፈቅሩ እንዲሁም ጥበበኞችና ተናግሮ አሳማኞች መሆን አለባቸው    
  • የሚመረጡት ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭውም ዓለም ከሚኖሩት መሆን ይገባዋል 
  • የሚመረጡት ግለሰቦች በሰላማዊ መንገድና በትጥቅ ትግልም ከሚታገሉ ድርጅቶችም መመረጥ አለባቸው። በትጥቅ ትግል ካሉት ድርጅቶች ውክልና እንደተገኘ የትጥቅ ትግላቸውን ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ለጊዜው ማቆም ያስፈልጋል 
  • የሚመረጡት ግለሰቦች በፖለቲካ ምክንያት በእስር ቤት ካሉትም ሊካተቱ ይችላሉ

ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አንዱ የሌላውን ጭራ ወይም ጅራት ይዟል አንዱ ቀድሞ ቢለቅ በሌላው ሊነከስ ይችላል ያለው አማራጭ ሁለቱም አካላት እጆቻቸውን ከጨበጧቸው ጭራዎች ላይ በአንድ ጊዜ በማንሳት እጅ ለእጅ ለመያያዝ ፊታቸውን ማዞር ነው እጅ ለእጅ ከተያያዙ መተያየት ይመጣል ከተያዩ ደግሞ መነጋገር ይችላሉ ከተነጋገሩ ደግሞ ወይ ወደጭራ መጨበጥ ለመመለስ ወይም ደግሞ ለመተቃቀፍ አለበለዚያም በመሃል ገላጋይ ለማስገባት ይችላሉ በዚህ ጽሑፍ የተነሳው ዋና ሀሳብ የሚያተኩረው ጭራን ለቆ እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ ዝግጅት ማድረግ ላይ ነው ዝግጅቱ እየተካሄደ ወይም ካለቀ በኋላ ግን መጨባበጥ ከዚያም መተቃቀፍ ሊመጣ ይችላል       

ከላይ የተጠቀሰው ልዩ ብሄራዊ ኮሚቴ ዋና ሥራው መጨባበጥና መተቃቀፍ የሚደረስበትን ምቹ መንገድ መጥረግ ነው መንግስት ልዩ ሓላፊነት ስላለበት በከፍተኛ የሞራል ልዕልና ላይ በመገኘት ኮሚቴውን ማገዝ አብሮም መሥራት ይኖርበታል ኮሚቴው ሥራውን እስኪያቀላጥፍ መንግስት ለለውጥ የምር እንደተነሳሳ ለማመልከት ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል የፖለቲካ እስረኞችን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት በትግሉ ሂደት ስለሞቱት ይቅርታ መጠየቅ የተጎዱት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ የመገናኛ ብዙኅንን ለህዝብ ፍጆታም እንዲውሉ መፍቀድ በነጻነት መናገርንና መጻፍን እንደገና ማበረታታት ወዘተ ሊሆን ይችላል ይህ ከተደረገ መንግስት ራሱን በአዲስ የታሪክ መዝገብ ላይ ያገኛል ራሱንና ህዝቡን ከጥፋት ያድናል እንዲህ በሥራ የሚገለጽ የለውጥ ፍላጎት ብዙ ድካምና ጣጣ ካለበት ብሄራዊ እርቅ ይልቅ አብዝቶ ይናገራል የቀደመ በደልንና ግፍን ይሽራል 

          
እኔ የምመኘው ይህን ነው ለውጡ ማንንም ሳያገልና ሳይበላ በንጽህና ይካሄድ ዘንድ! ይህን ለማድረግ ከፍተኛ የሞራል ልዕልናና ዲሲፕሊን ከሁሉም ወገን ያስፈልጋል። ይህ የሞራል ብቃት ከሌለ ግን ያቀረብኩት ሀሳብ እርባና የለውም። ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ አገሬ በሰላምና በአንድነት የምር ለውጥ ታመጣና ትጠብቀውም ዘንድ ስለምመኝ ይህን ብያለሁ። እናንተ ውድ አንባቢያን ደግሞ ከዚህ እጅግ የነጠረና ተግባራዊ የሆነ መፍትሔ ልታቀርቡ ትችላላችሁ!



ማሳሰቢያ- ሥዕላቱንና ፎቶዎችን የወሰድኳቸው ከተለያዩ  የፌስ ቡክ ገጾች ነው!

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...