Thursday 30 June 2016

ማኅበረ ቅዱሳንና ፈታኞቹ የመጨረሻው ክፍል

መግቢያ
ስለወቅታዊ ጉዳዮች ለመጻፍ ተነሳስቼ ነበር ዳሩ ግን ከዚህ በፊት ስለማኅበረ ቅዱሳን ሁለት ተከታታይ ጽሑፎችን አቅርቤ ሦስተኛውን እንደምቀጥልበት ቃል መግባቴ ትዝ አለኝ ጥቂት አንባቢዎቼም «እስካሁን የጻፍካቸው ሁለቱ ጽሑፎች መግቢያ ናቸው ዋናውን አስከትልና እንተያያለን ብለውኝ እንደነበርም ትዝ አለኝ እናም በሥራ ምክንያት አቋርጨው የነበረውን የጀመርኩትን ጨርሼ እጅግ ወቅታዊ ወደሆኑ ጉዳዮች ማተኮር እንዳለብኝ ወስኜ ይህን የመጨረሻውን ክፍል አቀረብኩበዚህ አጋጣሚ አስተያየት የሰጣችሁኝን ሁሉ ከልብ እያመሰገንኩ ወደ ክፍል 3 ላምራ!  

በክፍል 1 ጽሑፌ ስለማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ) መጻፍ ለምን እንዳስፈለገ ማኅበሩን እንዴት እንዳወቅኩትና ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የማኅበሩን አመሠራረትና ዓላማ በጥቂቱ አቅርቤያለሁ ክፍል 2 ደግሞ ማቅን አብዝተው የሚገዳደሩ አካላት እነማን እንደሆኑ በደረጃ ከነምክንያቶቻቸው አቅርቤያለሁ ይህ የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ማቅን እጅግ በላቀ ደረጃ የሚፈትኑ አራት አካላት ወይም ፈታኞች እነማን እንደሆኑና ምክንያቶቻቸውን አቀርባለሁበመጨረሻም የማጠቃለያ ሀሳብ አቀርባለሁ።

ይህ ጽሑፍ በክፍል 1 እንደተጠቀሰው በዋናነት ማቅንም ሆነ ሌላ አካልን ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ የተዘጋጀ አይደለም ያሉ እውነታዎችን ከግል እይታዬ በመነሳት በትንተና መልክ ለአንባቢ ማስገንዘብ እንጅበዚህ ጽሑፍ ምክንያት ሊነሱ የሚችሉ ውይይቶችና ሙግቶች በመጨረሻ የተሻለ ግንዛቤ እንዲመጣ ያደርጋሉ ብዬ አምናለሁ። ለማንኛውም ከዚህ በፊት በጨረፍታና በተዘዋዋሪ መንገድ ሲነሳ የነበረውን ጉዳይ ፊት ለፊት ለውይይት ማምጣቱ የተሻለ እንደሆነ እገምታለሁ   

በክፍል 2 እንደተገለጸው አገር ቤት ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ሙዘረኞች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ አገር ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ያሉ ካህናትና አገልጋዮች እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ለማቅ ልዩ ፈተናዎች ናቸው። ከሌሎቹ ይልቅ እነዚህ አራት አካላት ማቅን አስጨንቀው ይዘዋል። እነዚህን አካላት በይፋ ለመፋለም ማቅ የተቋቋመበት ዓላማ ስላልሆነ አስቸጋሪ ነው። ዝም እንዳይልም በኅልውናው መጥተውበታል። ማቅ እስካሁን ድረስ ስልታዊነትን ያገናዘበ አካሄድን በመምረጥ ለመቋቋም ሞክሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥንካሬ ያላቸውን መግለጫዎች በማውጣት ራሱን ከመከላከል ወደ ማጥቃትም መውሰድ እንደሚችል አመላክቷል። ለመሆኑ እነዚህ ፈታኝ አካላት እንዴትና ለምንድን ነው ማቅን ለማፈን የፈለጉት? 

ፓትርያርክ ብፁዕ አባ ማቲያስ

ፓትርያርክ አባ ማቲያስ በአሜሪካን አገር በስደት በነበሩባቸው ዘመናት እዚያ ካለው የማቅ ቢሮ  ጋር ተስማምተውና ተባብረው ይሠሩ እንደነበር ይታወቃል በለስ ቀንቷቸው የታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ ግን ቀኝ ኋላ በመዞር በይፋ ማቅን ለማሳቀቅ ለማኮሰስና ለማጥፋት ዘመቻ ከፈቱ በርካታ ከበድ ያሉ ርምጃዎችን ወሰዱ ማቅ በብዙ ድካም ያዘጋጃቸውን ጉባኤያት (ለምሳሌ የአብነት መምህራን ጉባኤና ወርኃዊ ጉባኤ) አስተጓጉለዋል የማቅን ህትመቶች እንዳይታተሙ በማገድ ሥርጭታቸውን አዘግይተዋል የማቅን መተዳደሪያ ደንብ እንዲያሻሽል በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየመውን ኮሚቴ አግደው የራሳቸውን ረቂቅ ደንብ አቅርበዋል።      

እንዲሁም የመምሪያና የደብር ኃላፊዎችን በመሰብሰብ በማቅ ላይ አሳምጸዋል:ለምሳሌ ያህል መስከረም 27 ቀን 2008 / በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ፣ መስከረም 29  ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ  የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች በታደሙበት ጉባኤ ላይ ፓትርያርኩ የአሠራር መዋቅርን ሳይጠብቁና የቅዱስ ሲኖዶስን ይሁንታ ሳያገኙ ቀስቃሽና ስሜታዊ የሆኑ ንግግሮችን አቅርበዋል ከዚህ ቀጥሎ  የተዘረዘሩት ማቅን በተመለከተ ቃል በቃል የተናገሯቸው ነጥቦች ናቸው

§  የሚሰማኝ ስላጣሁ ከበታች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር መወያየት አስፈለገኝ ወደፊትም ዓመቱን ሙሉ አደርገዋለሁ
§  ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ ነው የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሀብት ቀምቷል
§  ይህ ማኅበር በቁጥጥር ሥር እንዲውል አሳስባለሁ
§  እኔ ይኽን ጉዳይ ከራሴ አወርዳለኹ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘቧ፣ ክብሯ ተወስዷል 
§  ቤተ ክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ፤ ካህናቱ ከመከራ ይውጡ
§ይ ህችን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ፤ አንዷን ቅድስት፣ ኦርቶዶክሳዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ልመራ እንጂ ሁለት ቤተ ክርስቲያን የለችም
§  እኔ ብቻዬን የምሠራው ነገር የለም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ
§  በሕግና በሥርዓት የማይመራ ማኅበር አሸባሪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው
§  አባ ማትያስ አላበደም፤ መልእክቴን እያስተላለፍኹ ነው ያለኹት፤ መልእክቴን በጸጋ ተቀበሉ ብዬ እማፀናችኋለኹ

ባጠቃላይ ሲታይ ከነዚህ ድርጊቶች በመነሳት ፓትርያርኩ የማቅ ዋና ፈታኝ ናቸው ቢባል የከበደ አይደለም። በማቅ ላይ ፈተናውን እንደዚህ በይፋ ያከበደ ሌላ አካል ያለ አይመስልምለመሆኑ ማቅን ይህን ያህል ለመፈተን ለምን ፈለጉ? ይህ ጥያቄ ለቀጥታዊ መልስ የተመቸ ባይመስልም ከከባቢያዊ ክስተቶች በመነሳት አሳማኝ መላ ምት ማቅረብ ይቻላል

አንድ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ማቅ መገታት ከዚያም ፈጽሞ መመታት እንዳለበት ለፓትርያርኩ ሳይታክቱ የሚያሳስቡ አካላት እንዳሉ ይታመናል መንግስት የቤተ ክህነት አንዳንድ የመምሪያ ኃላፊዎችና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለማደስ የሚራወጡ ወገኖች ፓትርያርኩን በቅርብ ርቀት ሆነው ስለማቅ መዳከም እንደሚወተውቷቸው ከዚህ በፊት ልዩ ልዩ ዘገባዎች ጠቁመዋል የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም «እስርዎ እኛን የሥራ ባልደረቦችዎን ትተው ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጉ ጋር ይመክራሉ» ብለው ፓትርያርኩን ገስጸዋቸዋልተግሳጹን ተከትሎ ፓትርያርኩም ጥቂት አማካሪዎቻቸውን በተራቸው እንደገሰጿቸውና ከአበው የሲኖዶስ አባላት እንደለዩአቸው መናገራቸውን ሐራ ተዋሕዶ ዘግባ ነበር     

ሁለት የአመራር ብቃት ችግር ያለባቸውም ይመስላል ከላይ ነጥብ በነጥብ የዘረዘርኳቸው ፓትርያርኩ በስብሰባ ላይ ማቅን በተመለከተ የተናገሯቸው ንግግሮች ለዚህ ልዩ ማሳያ ናቸው። የፓትርያርኩ ንግግሮች ከአንድ መንፈሳዊ መሪ ሳይሆን ከለየለት አምባ ገነንና ስሜታዊ መሪ የተገኙ ይመስላሉ ከዚህ አኳያ ሲታይ ፓትርያርክ አባ ማቲያስ ማቅን ጭብጥ ርግጥ አድርገው ለመግዛት የፈለጉ ይመስላልይህ ካልተቻለ ግን ማቅን እንደሚያጠፉት በይፋ ተናግረዋል። ትልቁን የቤተ ክርስቲያን አጀንዳ  ከትልቁ የነገውን ከዛሬው ለይቶ የማስቀመጥና ቅድሚያ የመስጠት አቅም እንዳላቸው አላሳዩ ም

ሦስት ፓትርያርኩ ዘመናዊ ትምህርት የተማረው ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ያለውን ድርሻና ኃላፊነት እምብዛም የሚያምኑበት አይመስልምበሳቸው አስተሳሰብ ምሁራን የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት ብለው እንዲኖሩ ብቻ ይፈለጋል። ለዚህም እንደማሳያ እርሳቸው ባንድ ወቅት «ቤተ ክርስቲያን በባዮሎጅና በኬሚስትሪ አትመራም» «ቤተ ክርስቲያንን ጃኬትና ኮት ለባሽ አይመራትም» በማለት ማቅን በገደምዳሜ ለመሞለጭ ሞክረዋል። ማቅ ቀሚስ ለባሽ ዲያቆናት ቀሳውስት ቆሞሳት መዘምራን ሰባኪያንና መሪጌቶች ባጠቃላይ ሊቃውንትም እንዳሉት የረሱ ይመስላሉ ልክ እንደ ጥንቱ ወጣቱን አግልለው በድንግዝግዝ መጓዝ ይፈልጋሉወጣቱ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንደሚያገባው ለእድገትና ለለውጥም ከፍተኛ አቅምም እንዳለው ገና ያመኑበት አይመስልም። ባጠቃላይ ሃይማኖታዊና ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመውን እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አካል ወጣቱን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የተቸገሩ አቅምም ያነሳቸው ይመስላልበአንጻሩ ደግሞ ሙሰኞችንና ዘረኞችን የመታገስ እንዲያውም የመሾምና የማበረታታት አዝማሚያ አሳይተዋል።     

ሙዘረኞች

    እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን የሥራ ዘርፎች ሙሰኞችና ዘረኞች (ሙዘረኞች) እየተበራከቱ መጥተዋል። የፖለቲካ አቋም በመያዝ ልዩ ሃይማኖታዊ ዓላማ በማንገብ እና የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለመብላት ሲሉ ብቻ ቀሚስ ለብሰው ቆብ ደፍተው መስቀል ጨብጠው በቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተሰገሰጉ አሉ። አባት ሲሏቸው ወንበዴ የሆኑ አሉ። መነኩሴ ሲሏቸው ዘማውያን የሆኑ አሉ። አንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች የመምሪያ ኃላፊዎች የሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጆች በኢ-ክርስቲያናዊ ምግባር ተጠምደዋል። በጉቦ ይሾማሉ (ሾ ጠብቆም ላልቶም ይነበብ) በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዘርፋሉ የሚያጋልጧቸውን ሰዎች ያባርራሉ፣ ከደረጃና ከደመዎዝ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ወዳልፈለጉት ቦታ እንዲዛወሩ ያደርጋሉ፣ ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ እንዳይኖር ይጥራሉ፣ ይህ ሁሉ ሆኖ ከተጋለጡም ሌላ የሥራ መደብ በሌላ ቤተ ክርስቲያን ይሰጣቸዋል፣ ባጠቃላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ሥራ ሁሉ አይመቻቸውም

ይህን አሳፋሪ ሥራ ከሚቃወሙት አካላት መካከል ማቅ ግንባር ቀደም እንደሆነና መረጃና ማስረጃ እንደሚሰበስብ ከዚያም እንደሚያጋልጥ ይልቁንም ምእመናንን በትምህርት እንደሚያነቃ ያምናሉ በመሆኑም ማቅን ይኮንናሉ አመራሩን አባላቱን በቡድንም በተናጥልም ያስፈራራሉ ያሳቅቃሉ ያባርራሉ ከአገልግሎት ያግዳሉ ከመንግስትና ከክርስቲያኖች እንዲሁም ከአባቶች ጋር ያጋጫሉ። በመንግስት በኩል ካሉት ሙዘረኞችና ሌላ እምነት ካላቸው አካላት ጋር እንዲሁም ከፓትርያርኩ ጽ/ቤት ጋር ቅርብ ግንኙነትና ትብብር ስላላቸው በማቅ ላይ ሌላም የማይናቅ ተጽእኖ ማድረግ ይችላሉ። አብዛኛውን ሥራቸውን የሚያከናውኑት በስውርና በቋሚነት ስለሆነ የጥቃታቸው መጠን በቶሎ በግልጽ አይታወቅም። ሆኖም ግን በሁለተኛ ደረጃ ማቅ ንጹህ አየር እንዳይተነፍስ የሚያደርጉ አካላት እንደሆኑ ይገመታል።      

ስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ

መቀመጫውን በአሜሪካን አገር ያደረገው በብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና ካህናት ማቅን በበጎ ዓይናቸው አይመለከቱትም ማቅን እንደ ከሳሽ አጥቂና ተቀናቃኝ አካል ይቆጥሩታል የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆነም ላለማመን ይጥራሉ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንቅፋት እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ እንዲያውም ማቅን የነጋዴዎች ማኅበር የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲከኞች ስብስብ የሀሰተኞች ስብስብ ያላዋቂዎች ማኅበር ወዘተረፈ በማለት እውቅናን ይነፍጉታል። በቅርብ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ተሰጥቶት ስብሰባ ያደረገው የካህናት አንድነት ማኅበር ያወጣው የአቋም መግለጫ በግልጽ ማቅን ያወገዘና አብያተ ክርስቲያናት ማቅን እንዲያሳድዱ መመሪያ-ዘል ትእዛዝ የሰጠበት ነው።

ለመሆኑ ማቅ ውጭ ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ያህል የተጠመደው ለምንድን ነው? ምክንያቶች ቀጥለው ያሉት እንደሆነ ይታመናል አንድ ማቅ ጳጳሳት እንጅ ሲኖዶስ አይሰደድም ብሎ ስለሚያምን ውጭ ላለው ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናን አልሰጠም። ምንም እንኳን የማኅበሩ ወይም የአባላቱ የግል አቋም እንደሆነ በግልጽ መለየት ቢያቅትም አንዳንድ ታዋቂ የማቅ አባላት በአሜሪካና በአውሮፓ እየተዘዋወሩ የሲኖዶስን አንድነት ሰብከዋል። ሁለት የማቅ አባላት ገለልተኛ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን ወደ አገር ቤት ሲኖዶስ በማስገባታቸው የውጭው ሲኖዶስ ደስተኛ አይደለም። ይልቁንም ማቅን እንደ ተቀናቃኝ ያየዋል ቢባል አይከብድም።

ሦስት ቀላል የማይባል የማቅ አባላት በውጭ ሲኖዶስ ስር የተሐድሶ ትምህርትን የሚያሰራጩ ጥቂት ካህናትና ሰባኪያን እንዳሉ ያምናሉ። ይህንም በልዩ ልዩ መንገዶች ይገልጣሉ። እንደማስረጃም በአገር ቤቱ ሲኖዶስ መረጃና ማስረጃ ቀርቦባቸው አላምን ያሉና የተወገዙ አገልጋዮች የውጭውን ሲኖዶስ መቀላቀላቸውን ያነሳሉ። ከዚህም አልፎ ትውፊትንና ሥርዓትን የሚገዳደሩ ትምህርቶችን አንዳንድ አገልጋዮች በቋሚነት እንደሚያስተምሩ ያስታውሳሉ። ቅርብ ጊዜ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ መዘመርን በተመለከተ በሁለቱም ወገኖች በኩል የተደረጉ ክርክሮች ለዚህ ነጥብ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ባጠቃላይ ሲታይ በማቅና በስደተኛው ሲኖዶስ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት በአገር ቤቱ ሲኖዶስና በአሜሪካው ሲኖዶስ መካከል ካለው ተቃርኖ እምብዛም የተለየ አይመስልም።    

መንግስት

የኢትዮጵያ መንግስት ማቅን በከፍተኛ ጥንቃቄ ይከታተለዋል። በውስጥና በውጭ ሰላዮችን ያለማቋረጥ በመላክ ማቅን በቋሚነት እንቅልፍ ይነሳል። ሲፈልግ የማቅን ጉባኤዎች ስብሰባዎች ያግዳል። በመገናኛ ብዙኅን ማቅን ከአክራሪና አሸባሪ አካላት ጋር በገደምዳሜ ያነሳዋል። ማቅን ሰለፌ አጥባቂ ትምክህተኛ እያለ ያብጠለጥላል። የአመራር አባላቱን በልዩ  ልዩ መንገድ ያዋክባል።

መንግስት ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ምንድን ነው? አንድ መንግስት በባሕርይው የተጠናከረ ማኅበር ወይም ድርጅት የህልውናው ጸር እንደሆነ ስለሚያምን። ሁለት ማቅ የኢትዮጵያን ረጅም ታሪክ ያለምንም ፍርሃትና ስጋት ለወጣቱ በማስተማሩ። ሦስት ማቅ በብሄረሰብ ሳይሆን በብሄራዊ ደረጃ በመዋቀሩ። የማቅ ከፍተኛ አመራርና ተራ አባላት ከኦሮሚያ ከደቡብ ከምስራቅ ከሰሜንና ከመካከለኛው ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው። በመሆኑም ማቅ በልዩ ልዩ አገልግሎቶቹ ኢትዮጵያዊነትን እንጅ ዘውግን ባለማንጸባረቁ። አራት ማቅ በቤተ ክርስቲያንና በአገር ዙሪያ ያለውን ሙስናና አስተዳደራዊ ዝርክርክነትን በለሆሳስ ቢሆንም በመቃወሙበነዚህና  በሌሎችም ጉዳዮች ማቅ  የራስ ምታት በመሆኑ መንግስት አብዝቶ ይከታተለዋል ያስደነግጠዋል ይጎሽመዋል 

 

ማጠቃለያ

ከላይ እንደተመለከተው አብዛኞቹ የማቅ ወሳኝ ፈታኞች ማለትም ፓትርያርክ አባ ማቲያስ ሙዘረኞችና ስደተኛው ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካላት ናቸው የሚመስለውን ስለጻፈ ብቻ በእስር ቤት የሚሰቃየው ጋዜጠኛ ተመስገን ዘውዴ ባንድ ወቅት የማቅን ህልውና የሚፈታተነው መንግስት እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር ዳሩ ግን መንግስት ማቅን ውስጡን ገልብጦ በማጠብ ማንነቱን አውቋል ለመንግስት ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ አረጋግጧል በመሆኑም ማቅን ፈጽሞ ሊያጠፋው አይሻም ይህ ማለት ግን መንግስት ማቅ ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ጉሸማ ትቷል  ማለት አይደለም። ሌላ ማቅን ከፊት ሆኖ ሊያጠፋ የሚፈልግ አካል ካለም መንግስት አያበረታታም ማለትም አይደለም።

ይልቁንስ ማቅን ጠራርገው ሊያስወግዱት የሚለፉ አካላት ፓትርያርክ አባ ማቲያስ ሙዘረኞችና ስደተኛው ሲኖዶስ ናቸው እነዚህ አካላት ማቅን ለማድቀቅ ከዚያም ለማጥፋት ሥልጣንና አቅም እንዳላቸው ይናገራሉ እስካሁንም ማቅ በእጃቸው ያልጠፋው ኢትዮጵያ ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጸሎትና ተጋድሎ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ ዳሩ ግን የቅዱስ ሲኖዶስ የማስፈጸም አቅም ውሱንነትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚሾሙት አንዳንድ ጳጳሳት እውነትን የመኖር አቅም መዳከም ሲታይ ማቅ ወደፊት ይበልጥ አስጊ ጊዜያት እንደሚገጥሙት ይገመታል  

ማቅ እኒህን ፈታኞች ስልት ነድፎ አቅም አሰባስቦ በቀጥታ ለመቃወም የተሰጠው መብት ብዙም የሚፈቅድ አይመስልም። እንዲሁም ታላላቅ አባቶች ምንም ይሥሩ ምን እነሱን ለመተቸት ወይም ለመቃወም መሞከር በህዝቡ ዘንድ እስካሁን ድረስ ብዙም ተቀባይነት አላገኘም። ለዚህም ነው እነዚህ ሦስቱ አካላት የማቅ ልዩ የቤት ሥራው ናቸው ለማለት የደፈርኩት። እናም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ካለው ይልቅ በውስጧ የሚገኙት አካላት ለማቅ መኖርና አለመኖር ወሳኝነት አላቸው።

ሊመጣ ካለው ምት ሁሉ ይድን ዘንድ ማቅ አሠራሩንና ርዕዩን ከማኅበሩ አባላት ባሻገር በህዝብ ኅሊናና ልቡና ውስጥ ማስቀመጥ ይገባዋል። ይህንም ማድረግ የሚቻለው በኢትዮጵያም ሆነ በውጭውም ዓለም ከህዝብ ጋር በይፋ የሚያገናኙትን ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን መፍጠር ሲቻል ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን መልካም ሊባል የሚችል ግንኙነት አጠናክሮ  መቀጠል ሃይማኖታዊ ግዴ ስልታዊም ነው።

እንዲሁም ማቅ ከስደተኛው ሲኖዶስ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊፈትሽና የአገልግሎቱንም ተደራሽነት ሊመረምር ግድ ይለዋል። በሥራቸውና በእምነታቸው እንቅፋት የሆኑ ሰዎች ካሉ እነሱን ከቅዱስ ሲኖዶስ ለይቶ መቃወሙ ውጤታማ ያደርጋል። እንዱሁም የማኅበሩና የአንዳንድ አባላቱ አስተዳደራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሏቸው አቋሞች ተለይተው መቀመጥና ለተፈጻሚነታቸውም ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል። ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለት ከሆነ በኋላ አንድ ነው እያሉ መከራከር በሚሊዮን የሚቆጠረውን በውጭ አገራት ተበትኖ አገልግሎት የሚናፍቀውን ምእመን እንደመርሳት ይቆጠራል።

ስደተኛው ሲኖዶስም በደምሳሳው ማቅ መሰሪ እንደሆነ ከመለፈፍና ከማውገዝ ይልቅ በማቅ የተሠሩ ጥፋቶች ካሉ ነቅሶ በማውጣት ክርስቲያናዊ በሆነ ቋንቋና ባህል መዳኘት ያስፈልጋል። ማቅን ከኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ደርቦ መምታት ወጣቱንና የተማረውን አማኝ ማሳደድ የነገዋን ቤተ ክርስቲያንንም እንደማኮሰስ ይቆጠራል። በሚደረገው ማናቸውም ፍጥጫ በሚሊዮን የሚቆጠረው ስደተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ግራ እንደሚጋባ መታወቅ አለበት። ማንም ለማንም መሰናክል ከሚሆን ይልቅ በአንገቱ ላይ ድንጋይ አስሮ ራሱን ወደጥልቁ ቢወረውር እንደሚሻለው ቅዱስ ወንጌል አስጠንቅቋልና።               


///////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////
   


No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...