Saturday 7 June 2014

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል? ክፍል 2

በክፍል አንድ ጽሁፌ ብዙ ኢትዮጵያዊ በቂ የአገር ስሜት እንደሌለው ሞግቻለሁ:: አገራዊ ስሜት ማለትም አገራችንን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም ጠቁሜአለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ የአገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች እንደሆኑም ለምሳሌነት አንስቻለሁ:: ከዚያም አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ማንሳትና መወያየት ፖለቲካዊ ንቃተ ኅሊናን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሳስቤአለሁ:: በዚህ ጽሁፍ ሁለት ለአገራዊ ስሜት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ተጠቃሽ መንስኤዎችን ወይም ምክንያቶችን ለውይይት አቅርቤአለሁ::   

ባህላዊ አስተምህሮአችን 

ባህላችን የማንነታችንና ምንነታችን መገለጫ ነው:: ይሁን እንጅ ባህል ሁሌ ጠቃሚ እሴችን ብቻ ሊይዝ ሊያስተላልፍ አይችልም:: በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ጎጅ ትምህርቶች ልምዶችና ወጎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ:: በመሪና በተመሪ መካከል ስላለው ግንኙነት ብንመለከት ብዙ ጎጅ የሆኑ አመለካከቶችን እናገኛለን:: 

ማንኛውም ዜጋ ለመሪው ወይም ለመንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መታዘዝና መገዛት እንዳለበት ለበርካታ መቶ ዓመታት ተሰብኳል:: መሪዎች ወይም መንግስታት ህግ ቢተላለፉ ማንም መጠየቅ እንደማይችል በአንድም በሌላም ዘዴ ተነግሯል:: ለዚህም "ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ" የሚለው አባባል ጥሩ ምሳሌ ነው:: እንዲያውም ህዝቡ ወይም ተመሪው ለመሪው ያለመታተክ የመገዛት ሃይማኖታዊና ተፈጥሮአዊ ግዴታ እንዳለበት ይነገረዋል:: መንግስት ጌታ ሲሆን ህዝብ ደግሞ ባሪያ ነው:: ባሪያ የሚፈቀድለት ነገር ቢኖር የጌታውን ደህንነት መጠበቅና የሚፈልገውን ማድረግ ነው:: ህግጋትና ሥርዓታት ሁሉ የተዘጋጁት ለባሪያው እንጅ ለጌታው አይደለም:: ጌታው ከህግ በላይ ነው:: ጌታው የህዝቡን ንብረት የመውሰድ መብት አለው:: ፖሊሱ ሚሊሻው የደህንነት ሠራተኛው ወታደሩ አልፎ አልፎ የውጭ ጠላት ካልመጣ በስተቀር በዋናነት የሚያገለግለው ጌታውን ነው:: ይህንን ያልተጻፈ ህግ ከወላጆቻችን እየሰማን በአይናችንም እያየን አድገናል:: አውቀንም ሳናውቅም ህጉን እንፈጽማለን:: አንድ መንግስት የፈለገውን ያህል ጨቋኝ ቢሆን የእኛ መልስ ጸጥታ ነው:: መንግስቱ ለ17 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጦ ሲገዛን ምላሻችን ዝምታ ነበር.: የአሁኑ መንግስትም ራሱ ያወጣውን ህግና መመሪያ ለእኛ ባሪያዎቹ ጥሎ እርሱ ከህግ በላይ ከሆነ ሁለት ዓስርት ዓመታት አለፉ:: ጥረን ተጣጥረን ያደረግነው ቢኖር በጣት የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረግ ብቻ ነው:: አብዛኛው ሰው በጸጥታ ባሪያነቱን ተቀብሎ  እንደሚኖር ለማሳየት ነው እንጅ የተወሰኑት ቆራጦች ዕለት ከዕለት ያደረጉትን ትግል እረስቼ ግን አይደለም:: 
   
ለዚህ ጎጅ ባህል መዳበር በግንባር ቀደምትነት የሃይማኖት ተቋማትን ተገን ያደረጉ ልሂቃን ተጠቃሽ ናቸው:: በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖቶች ይህ ጉዳይ አለ:: የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ለመከላከል በተደረጉ መራራ ትግሎች ወሳኝ ሚና ተጫውታለች:: ኢትዮጵያዊ ወኔ እንዲዳብርም ሁሌ ትሰብካለች:: ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መንግስታትና መሪዎች ህግን እንዲያከብሩና ህዝቡን በማስተዋል እንዲመሩ ግን ያደረገችው አስተዋጽዖ የጎላ አይደለም:: እንዲያውም አንዳንድ መምህራን ወቅቱ ላመጣው የመንግስት ሥርዓት ሁሉ ህዝቡ በአንክሮ መገዛት እንዳለባቸው  ያስተምራሉ:: በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አማኙ ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ስለሳውዲ ዓረቢያ እንዲያስብና እንዲብከነከን ያስተምራሉ:: ከፕሮቴስታንት አስተማሪዎች የሚሰማው ደግሞ  ስለጌታ አዳኝነት ብቻ እንጅ ስለኢትዮጵያ ህዝብና ችግሩ አይደለም:: 

በአጠቃላይ ሲታይ ህዝቡ በየጊዜው በለስ ለሚቀናቸው መንግስታት እና መሪዎች ያለምንም ጥያቄ እንዲታዘዝ ተነግሮታል:: የፖለቲካ መሪዎች በህዝቡ ላይ በደልና ግፍ ሲፈጽሙ የትኛውም የሃይማኖት ተቋም ተቃውሞ አያነሳም:: ህግና  እውነት እንዲጠበቅ ከመስበክ ይልቅ ህዝቡ መሪዎችን አፍሮና ፈርቶ እንዲኖር ይነገረዋል:: እንዲያውም ከበዳይ መሪዎች ጎን በመቆም ህዝባቸውን የሚያሳዝኑም የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች አሉ:: አሁንማ  ይባስ ብሎ ጨቋኝ የሃይማኖት መሪዎችንም እያየን ነው:: ይህ ጎጅ ባህል ለዘመናት እየተንከባለለ 21ኛው ክፍለ ዘመን ደርሷል:: ብዙ ሰው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርግ በተለያዩ መንገዶች አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ይገኛል:: ይህን ስል ግን የተጠቀሱት የሃማኖት ተቋማት ጭቆናን በአቋም ደረጃ ይደግፋሉ ማለቴ አይደለም:: እነሱን ተገን ያደረጉ አስተማሪዎችንና መሪዎች የሚሰሩት ሥራ እንደሆነ ግን  ይሰመርበት::        
             

ፍርሃትና ስጋት

የኢትዮጵያን ህዝብ ጀግንነት መላው ዓለም ጠንቅቆ ያውቀዋል:: የዓረብና የአውሮፓ ወራሪዎችን ቅስም ሰብሮ አባሯል:: ኢትዮጵያ በማንም አገር ቅኝ እንዳትገዛ አድርገዋል:: ይህ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ከሚያስችሉን ታሪኮቻችን ውስጥ ትልቁ ነው:: ወደፊትም ይህን አይበገሬነታችንን ይዘን እንደምንቀጥል ተስፋዬ ነው::  

ነገር ግን የህዝቡ ጀግንነት ጎልቶ የሚታየው ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በሚደረገው ግብግብ ብቻ ይመስላል:: ከባእዳን ያልተናነሱ ግን በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጨቋኝ መሪዎቻቸውን ግን የሚፋለሙበት ወኔ የሚያንሳቸው ይመስላል:: ለዘመናት በነጻነት ኖረናል ይባላል እንጅ ለአፍታም ቢሆን እያንዳንዱ ዜጋ መብቱና ጥቅሙ ተከብሮለት ኖሮ አያውቅም:: ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ህዝቡ ለመንግስታቱ ያለው ፍርሃት ግን ዋናው ነው:: ውስጥ ለውስጥ በጥንቃቄ ከሚነገር ሃሜት አልፎ ጨቋኝ መሪዎችን በይፋ የሚያወግዝበትና የሚጠይቅበት ድፍረት ያጣ ይመስላል:: በአገር ቤትም ይሁን በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ድፍረትና ግልጽነት ባለው መልኩ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢና አሳፋሪ ሁኔታ መናገር ሲያሸማቅቃቸው ይታያል:: ለምን ያለውን የመብት መጣስና ቅጥ ያጣ ድህነት መናገር እንደማይፈልጉ  ሲጠየቁ የብዙዎች መልስ "እባክህ ልኑርበት" ሆኗል:: በስብሰባዎችና በውይይቶች መሳተፍ ባድሜና ዛላንበሳ እንደመዝመት አስፈሪ እየሆነ ነው:: ብዙዎች በፍቅርና በተመስጦ የሚወያዩባቸው ጉዳዮች ስፖርትና ሙዚቃ እንዱሁም አገር ቤት ህንጻ ስለመገንባት ሆነዋል:: 

ብዙዎች ፍርሃታቸው መጠን ከማጣቱ የተነሳ የራሳቸው መብትና ጥቅም ሲነካ እንኳን አይቃወሙም:: ስለህዝባቸው መቸገርና መጨቆን የሚታገሉትን ሳይቀር ፈርተው ለማስፈራት ይጥራሉ:: ተቆርቋሪ ወገን በመሆን ለመብት የሚታገሉትን ያስጠነቅቃሉ:: "አገር ቤት የጀመርከውን ቤት ሰርተህ ብትጨርስና በሰላም ብትኖርበት ይሻልሃል" የሚል ምክር ጣል ያደርጋሉ:: መንግስት ያለውን የካድሬ ብዛትና የስለላ መረብ  እንዲሁም እየሰጠ ያለውን ጽኑ ቅጣት ለማስፈራሪያነት ያነሳሉ:: በአንድ ወቅት አርቲስት ታማኝ በየነ እንዳለው ሌሎች ለሚጽፉትና ለሚናገሩት የሚያነቡትና  የሚሰሙት እየፈሩ ነው:: አንድ በስድሳዎቹ የእድሜ ክልል ያሉ አባት ይህን ቅጥ ያጣ ፍርሃት በተመለከተ ያጫወቱኝን ላካፍልና የዛሬውን ጽሁፌን ላጠቃልል:: 

በፈታኙ የደርግ ጊዜ ነው:: እኒህ የሃይማኖት ሊቅ የሆኑ አባት ኢሰፓዎችን ሳይፈሩ በህዝብ ፊት ይገስጹ ነበር:: አገዛዛቸውን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር:: በዚህም የተነሳ አብዮታዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ተወስኖም ነበር:: ይህን ሁኔታ የሚያውቁ ሌላ የሃይማኖት አባት በአንድ ወቅት እኒህን አባት አዲስ አበባ መንገድ ላይ ያገኟቸዋል:: ሰላምታ ከተለዋወጡና ጥቂት ከተነጋገሩ በኋላ "ይህን ድፍረትዎን አልወደድኩልዎትም ይጠንቀቁ" ይሏቸዋል:: እኒህ ሊቅ አባትም "እኔ ደግሞ የእርስዎ ፍርሃት ያስጠላኛል" ብለዋቸው ተለያዩ:: እስካሁን ድረስ እኒህ ጀግና አባት ለእውነት ሲታገሉ አሉ:: ስንቶቻችን ፈርተን ስንቶችን አስፈርተን ይሆን? ስንቶቻችንስ በፈሪዎች ምክር መሳይ ንግግር ተደናግጠን ሩጫችንን  አቁመን ይሆን? 

///////////////// ይቀጥላል ////////////////        
    
 

2 comments:

  1. I ppay a visit each day some logs and sites too read content, except this website
    gives quality based posts.

    ReplyDelete
  2. Hei Teklu,

    You have raised very good and interesting Points. Thank you for that. However, you did not mention about the real situation specially in the diaspora. Yes, there are many who are hero and who are commited to contribute their share and to Express their toughts. The problem is that the presense of the unbbelievable number of Groups (political, relegious, etc.) With different views and directions. Such problems have, I believe, contributed a lot in discouraging comitted People to contribute what they can. I hope you will come up With Your comment in line With this.

    Keep t up

    ReplyDelete

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...