Tuesday 3 September 2013

የትግራይ ህዝብ ሥጋትና የህወሓት ፖለቲካ

የትግራይ ህዝብ ከኢሕአዴግ መንግስት ምን ተጠቅሟል? የትግራይ ህዝብና መንግስት ምን አይነት ግንኙነት አላቸው? እነዚህንና ተያያዥ ጥያቄዎችን በተመለከተ አብርሃ በላይ ከመቀሌ አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል:: አብርሃ እንደመነሻ ያደረገው ከአንድ የትግራይ ተወላጅ የቀረበለትን ጥያቄ ነው::  ጥያቄውም ይህ ነው:: “ኢህኣዴግን ትቃወማለህ፣ ግን ህዝብን ለለውጥ ኣነሳስተህ ከህወሓት የባሱ ፅንፈኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ስልጣን ቢይዙስ ??? ስትቃወም ስለዉጤቱም ማሰብ ኣለብህ። በምትፅፋቸውን ነገሮች ለአዳንድ የትግራይ ጠላቶች መጋበርያ እየሆንክ ነው።”



መልስ

ሁሉም ዜጋ (የገዢው ፓርቲ ደጋፊም ተቃዋሚም) መጠየቅ ያለበት (የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ባህሪያዊ ሂደት መሆኑ ተገንዝቦ) በኢህኣዴግ እጅ ያለው ስልጣን (በለውጡ ሂደት) ‘ለማን ይሰጥ’ የሚለውን ነው። ሁለት ስልጣን ለመቀበል ያሰፈሰፉ ሃይሎች ኣሉ፤ (1) የኢትዮዽያ ህዝብና (2) ስልጣን በሃይል ለመያዝ የጓጉ የፖለቲካ ቡድኖች።

ኣንድ

እኔ ታድያ ‘ስልጣን ለኢትዮዽያ ህዝብ መሰጠት ኣለበት’ ከሚሉ ሰዎች ጎራ ነኝ (የምቃወምም ለዚህ ነው)። ምክንያቱም ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ዲሞክራሲን ማስፈን ነው። በዲሞክራሲያዊ መንግስት ህጋዊ ተቃዋሚዎች ይበረታታሉ፣ ኣማራጭ ፖሊሲያቸው ለህዝብ እንዲያቀርቡ ነፃ ሚድያ ይኖራል። ህዝቦች በነፃነት የፈለጉትን ፓርቲ ይመርጣሉ፤ ድምፃቸውም በገለልተኛ የምርጫ ቦርድና የፍትሕ ኣካላት መኖር ይከበራል። የህዝብ ድምፅ ከተከበረ ሲቪላዊ መንግስት የማቋቋም ዕድል ይኖራል። በዚ መንገድ በሃይል ስልጣን ለመያዝ የሚቋምጡ ሃይሎች ቦታ ኣያገኙም። ዓፈናው ከቀጠለ ግን ….
ዲሞክራሲ ማስፈን የብዙ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል። የ’ኣፍርሶ መገንባት’ ስትራተጂ ዕዳ ይቀንሳል። ደም ማፋሰስ ያስወግዳል። ኧረ ሲንቱን …… ህወሓት/ኢህኣዴግ ኣሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ማድረግ የሚችለው ትልቁ ኣስተዋፅኦ ዲሞክራሲን በማስፈን ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ነው። የትግራይ ህዝብ ትግልም ለውጥ ኣመጣ እንላለን።
በኢትዮዽያ ታሪክ (እስከ ኣሁን ድረስ) ስልጣን የተያዘው በህዝብ ፍላጎትና ምርጫ ሳይሆን በጠመንጃ ኣፈሙዝ ነው። ፓርቲዎች ተጠናክረው ስልጣን መያዝ ከቻሉ ለመጀመርያ ግዜ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ተግባራዊ ያደርጋሉ (የኢትዮዽያ የፖለቲካ ታሪክ ይቀይራሉ) ። ሰለማዊ ሽግግር ተደረገ ማለት ደግሞ ስልጣን ወደ ህዝብ ወረደ ማለት ነው። ህዝብ የስልጣን ባለቤት ከሆነ የመንግስት ኣካላት የሰው ጌቶች ሳይሆኑ የሰው ኣገልጋዮች ሆኑ ማለት ነው። በዚህ መልኩ የህዝቦች ነፃነት ተከበረ ማለት ነው፤ ቀጥሎም እኩልነት፣ ኣንድነት፣ መከባበር ይኖራሉ። እኛም ተዋደድን። ስለዚ ፓርቲዎች ሊከበሩ ይገባል።
ህወሓቶች የስልጣን ዕድሜ ማራዘም መፍትሔ እንዳልሆነ መገንዘብ ኣለባቸው። የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ድጋፍ ማሰባሰብ ዘለቄታ ያለው የህዝብ ደህንነት ዋስትና ሊሆን ኣይችልም። የህዝብ ዋስትና ዲሞክራሲያዊ (ጠንካራ፣ ነፃና ገለልተኛ) ተቋማት ናቸው። መሪዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ ሲሄዱና ሲመጡ እንደ ድልድይ ሁኖው በማገልገል ለህዝብ ደህንነት ዋስትና (ወይ ጋሻ) የሚሆኑ እነዚህ የፍትሕ ተቋማት ናቸው።

ሁለት

ህወሓት /ኢህኣዴግ የያዘውን ስልጣን በፍቃደኝነት (በምርጫ) ለህዝብ ካላስረከበ በሃይል እስኪወርድ ድረስ በስልጣን ይቆያል ማለት ነው። ይህንን የሚያሳየን ህወሓት ስልጣኑን ለሌላ ታጣቂ (ተዋጊ) ሃይል እንጂ ለህዝብ ለመስጠት ፍላጎት የለዉም ማለት ነው።
ሌላ የታጠቀ ሃይል ስልጣን ከያዘ ሌላ ህወሓት /ኢህኣዴግ መጣ ማለት ይሆናል። ምክንያቱም ስልጣን በሃይል ለመያዝ ሰው መግደልን ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ ወንጀሎች ይሰራሉ፣ ግድያ ይኖራል። (ሃይል ስንጠቀም ወንጀሎችም ይኖራሉ ኣለበለዚያ ግን ለውጡ የመጣው በሃይል ሳይሆን በሰለማዊ መንገድ ነው ማለት ነው)። እነዚህ የተወሰኑ ወንጀሎች ለመሸፈን ሲባል ሌሎች ተጨማሪ ወንጀሎች ይፈፀማሉ። እነዚህ ወንጀሎች እንዳይጋለጡ ለማድረግ (ጉዳቸውን እንዳይወጣ) ስልጣን የያዘውን የፖለቲካ ቡድን የራሱ ዳኞች፣ ወታደራዊ መኮነኖች፣ የደህንነት ሃላፊዎች ወዘተ ይኖሩታል።
ከተሸናፊው የፖለቲካ ድርጅት ‘ደህንነታዊ ስጋት’ በመስጋትም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በጠላትነት ይፈርጃል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ሌላ የኣደረጃጀት ኣማራጭና የፖለቲካ ስልት ያፈላልጋሉ። የሃገር ኣንድነትም ኣደጋ ላይ ይወድቃል።
ስልጣን ላይ የወጣ ሃይል ድክመቱን ለመሸፈን ሲል የሚጠራጠራቸውን ህዝቦች ለመቆጣጠር (የመገንጠል ጥያቄን በሃይል ለመመለስ) እንዲችል ኣሻንጉሊት ድርጅቶችን ያቋቁማል። ይህንን ሁኔታ ሌላ ኢህኣዴግ ያደርገዋል። እኛ ደግሞ “ኣዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ …” እንዘፍናለን።

ሦስት

በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ህዝቦችን የመጨቆን ዕድሉ ይቀንሳል። ምክንያቱም ፖለቲከኞቹ ከወንጀል ነፃ የመሆን ዕድል ኣላቸው። (ከወንጀል ነፃ ካልሆኑ ኣይመረጡማ) ወይም ከስልጣናቸው ለማውረድ ቀላል ይሆናል። እነሱም ከስልጣን መውረድን የሞትን ያህል ኣይፈሩም (በህዝብ የተመረጡ ናቸዋ)። ስልጣን ላለመልቀቅ ኣያንገራግሩም (ህዝቡ ሰልፍ ይወጣላ)። መሪዎቹ ሰልፍ ለወጣ ህዝብ እንዲገድሉ ወታደሮቻቸውን ኣያዙም። ምክንያቱም በፖለቲከኞችና ወታደሮች መሃከል (ህገ መንግስታዊ ከሆነ በቀር) ልዩ ግንኙት ወይ ትስስር ኣይኖራቸውም።
በህዝብ የተመረጡ መሪዎች ተጠያቂነታቸው ለመረጣቸው ህዝብ ይሆናል (የስልጣን ምንጫቸው ህዝብ ነውና)። ስልጣን የያዙት በሃይል ከሆነ ግን ተጠያቂነታቸው ለጠመንጃቸው ነው። የህዝብ ጉዳይ ኣያሳስባቸውም። ስለ ካድሬዎቻቸው እንጂ ስለ ህዝቡ ችግር ላይጨነቁ ይችላሉ።

ኣራት

ኢህኣዴግን መቃወም ለምን???

(1) ገዢው ፓርቲ ስልጣን ወደ ህዝብ እንዲመልስ ለማገዝ ያስችላል። ኢህኣዴግ የህዝብን ድምፅ ኣላከበረም፣ ህዝብ እየገዛ እንጂ እያስተዳደረ ኣይደለም ያለው። ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንፈልጋለን። የሁሉም ህዝቦች ደህንነትና ልማት የሚረጋገጠው ዲሞክራሲያዊ ነፃነት ሲፈቀድ ነውና።
(2) ኢህኣዴግ ችግሮቹን እንዲያርም ለማድረግ ነው። የመናገር መብት ያፍናል፤ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም ሌሎች ህዝቦች ይጨቁናል፤ ለራሱ ጥቅም ሲባል ኣሻንጉሊት ድርጅቶች በማቋቋም የሚገዙትን ህዝብ የማይወክሉ መሪዎች በኣስገዳጅነት እንዲገዙ ያደርጋል። እነዚህ ህዝቦች ራሳቸው ይወክሉናል ብለው በመረጡዋቸው ድርጅቶች መተዳደር ኣለባቸው። ህዝቦች በሚወክሉዋቸው መሪዎች ሲተዳደሩ የትግራይ ህዝብ ቢጠቀም ‘ጂ ኣይጎዳም።
(3) ለውጥ ፈልገን ነው። ለውጥ የመፈለግ ኣባዜ የተፈጥሮ ጥሪ ነው። እያንዳንዱን ትውልድ የራሱ /ለራሱ የሆነ ለውጥ የማምጣት ወይም የማድረግ የግል የቤት ስራ ኣለው። የኣባቶቻችን ታሪክ ለኛ (የኛ) ሊሆን ኣይችልም። ስለዚ ለውጥ መፈለግ በራሱ ስሕተት ኣይደለም። ለለውጥ መነሳት የህይወት ግዴታችን ነው።

ኣምስት

የትግራይ ስጋት የሚመነጨው ከነዚህ ዲያስፖራ ፖለቲከኞች ከሚያራምዱት ኣስተሳሰብ እንደሆነ ተነግሮኛል። እነዚህ የ ‘ትግራይ ጠላቶች’ እንደሆኑ ተደርገው የሚታሰቡ ሃይሎች መነሻቸው ምንድነው ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
እነዚህ ሰዎች በኢህኣዴግ መንግስት በጠላትነት ተፈርጀው ‘ኣሸባሪ’ ተሰይመው ከሃገራቸው የተባረሩ ናቸው። ከሃገራቸው ከተባረሩ ታድያ እንዴት ለህወሓት ጥሩ ኣመለካከት ሊኖራቸው ይችላል? በህወሓት ዘመነ መንግስት ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ካልተፈቀደላቸው ሃገራቸውን ለመግባት ህወሓትን በሃይል ማስወገድ ግድ ሊላቸው ነው። ስለዚ ጥረታችው ኣይደንቀኝም።
ጥያቄው እነዚህ ሰዎች ለምን የትግራይን ህዝብ target ያረጋሉ የሚል ነው። መልሱ ግን ቀላል ነው። (1) ህወሓት ራሱ … ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ኣንድ እንደሆኑ ኣድርጎ ይሰብካል (ድጋፍ ለመሰብሰብ)።
(2) የዲያስፖራው የፖለቲካ ስትራተጂ ተደርጎ ይወሰዳል። የትግራይን ህዝብ target ሲያደርጉ የትግራይን ህዝብ ፈርቶ ህወሓትን ከመደገፍ ይቆጠባል ከሚል ኣስተሳሰብና ከትግራይ ህዝብ ውጭ ያለው ኢትዮዼያዊ ‘በኣንድነት በመቆም’ ህወሓትን ከስልጣን ለማውረድ እንዲነሳ ታስቦ ነው።
(3) ተሳዳቢዎቹ ዲያስፖራ ኣራት ዓይነት ናቸው።
(ሀ) የፖለቲካ ብቃት የሚያንሳቸው (ህዝብና ገዢው ፓርቲ መለያየት ያቃታቸው ወይም መለያየት ያልፈለጉ)። እነዚህ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ህወሓትን ያግዛሉ። የትግራይን ህዝብ ሲሳደቡ , የትግራይ ተወላጆችም ሳይፈልጉ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፉ ይገደዳሉ። ግን ስጋት ሊሆኑ ኣይችሉም ስልጣን ኣይዙምና (በሃይል ካልሆነ በቀር)፤ የፖለቲካ ዕውቀት ፤ስለሚያንሳቸው ።
(ለ) ወደ ሃገራቸው እንዳይገቡ የተከለከሉ (በሰለማዊ መንገድ እንዲታገሉ በህወሓት ያልተፈቀደላቸው)። እዚ ላይ ስጋት ፈጣሪው ህወሓት ራሱ ነው።
(ሐ) በሻቢያ ተልከው ኢትዮዽያን ለመበጥበጥ ተከፍሎቸው የሚሰሩ (ኣብዛኞቹ ኤርትራውያን ናቸው)። ኢትዮዽያውያን ካልተባበርናቸው የትም ኣይደርሱም።
(መ) ከህወሓቶች ጋ ግንኙነት ያላቸው …. ይህንን ስትራተጂ ‘ዲያስፖራ ፖለቲከኞች ጥላቻ የሚሰብኩ ናቸው’ ተብለው እንዲፈረጁና የትግራይ ህዝብ እነሱን ፈርቶ ና ሰግቶ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፍ ለማድረግ የታለመ ነው።
ስለዚህ ጥላቻን የሚሰብኩ ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ሃገራቸውን እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ህዝባቸውን ለለውጥ እንዲያነሳሱ ቢደረግ የትግራይ ህዝብ የሚያዋሩዱበት ምክንያት ባልኖራቸው ነበር። ስለዚ የትግራይ ስጋት ሆን ተብሎ በህወሓት የተቀናበረ ነው።

ስድስት

ስጋቱ ቢኖርስ??? መፍትሔው በህወሓት እጅ ነው። ሥጋቱን ለመቀነስ ራሳችን የሌሎች ህዝቦች ስጋት ፈጣሪ መሆን የለብንም። እንደ ኣሰራርም :
(1) ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም ሌሎች ህዝቦች መጨቆን እንዲሁም ስጋት መፍጠር የለበትም። (ካልጨቆነ ስጋቱ ኣይኖርም)። ከዚህ ኣልፎም የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮዽያ ህዝቦች በሰላም መኖር የሚፈልግ እንጂ የህወሓት የጥላቻ ፖለቲካ እንደማይደግፍ በግልፅ መናገር ኣለበት። ይህ ካልሆነ ደግሞ መፍትሔው መደራጀት እንጂ ስልጣን የሙጥኝ ይዞ ህዝቦችን መጨቆን ኣይደለም።
(2) ህወሓት ዲሞክራሲን ማስፈን ሲገባው የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ስልጣን መጋበዝ የለበትም። ህወሓት ህጋዊና ሰላማዊ የተቃውሞ ድርጅቶችን ሲያዳክምና ሲያፈርስ ስልታቸውን ቀይሮው የሃይል መንገድ ተከትለው ከስልጣን እንዲያወርዱት እየጋበዛቸው ነው። ይህ ኣካሄድ ደግሞ ህወሓት በሌሎች ህዝቦች እንዳደረገው ሁሉ ኣሻንጉሊት ድርጅት መስርተው የትግራይን ህዝብ ለመጨቆን ያስችላቸዋል።

ሰባት

“ለአዳንድ የትግራይ ጠላቶች መጋበርያ እየሆንክ ነው” የሚል ነገር ኣለ። የትግራይ ጠላት ማነው? እንደኔ እምነት: የትግራይ ህዝብ ጠላት ጭቆና ነው። ጠላቶቹ ጨቋኞቹ ናቸው። ድሮ ደርግ ነበር ጨቋኝ፣ ኣሁን ደግሞ ህወሓት። ስለዚህ የትግራይ ጠላቶች ጨቋኝ ገዢዎቹ እንጂ ሌሎች ብሄሮች ወይ ሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ኣይደሉም።
ተጋሩ (የትግራይ ተወላጆች) የራሳቸው የፖለቲካ ኣቋም ይዘው ገዢውን መደብ ሲቃወሙ ‘ከጠላቶቻችን ኣብረዋል’ ወይ ‘ለጠላቶቻችን ያጋሉጥናል’ በሚል ሴራ በመንግስት ደጋፊዎች ይወቀሳሉ፣ ይገለላሉ። ግን እንዲህ ከተነቀፉኮ የትግራይ ተወላጆች የመቃወም መብት የላቸውም ማለት ነው። (ወይም እንዲቃወሙ ኣይፈቀድላቸውም ማለት ነው?)
በዚህ መልኩ (ተጋሩ የመቃወም መብታቸውን ከተገደበ) ‘ከትግራይ ወጥቼ ለትግራይ እቆማለሁ’ የሚል የህወሓት ድርጅት ፀረ ተጋሩ እየሆነ ነው ማለት ነው። ህወሓት ለትግራይ ቢቆም ኑሮ እኛ ተጋሩ የፈለግነውን የፖለቲካ ኣመለካከት እንድነራመድ ለምን ኣይፈቅድልንም? ደርግ ኣፈነን። ህወሓትም እንዲህ ካፈነን፣ ህወሓት ከደርግ (ለትግራይ ህዝብ) በምን ይሻላል? በምንስ ይለያል???
ህወሓት የመናገር መብታችን ካላከበረ፣ ሁሉም የትግራይ ሰው በእኩል ዓይን ካልታየ፣ በተግባሩና በስራ ኣፈፃፀሙ መመዘን ሲገባው በጎጠኝነት በስራው ግልፅ የሆነ ኣድልዎ ከተፈፀመበት፡ ከዚህ በላይ የህዝብ ጠላትነት ከየት ሊመጣ ነው? የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ሌላ ህዝብ በነፃነት ሓሳቡ የመግለፅ መብት ኣለው፤ ሊከበርለትም ይገባል።
ህይወቱ ሙሉ ከጭቆና ነፃ ለመውጣት ሲታገል የኖረ ህዝብ የእኩልነት መብቱ ሲነፈግ እኛ ዝም ብለን ሳንቃወም ማየት ነበረብን? ብዙ መስዋእት የተከፈለበት የ17 ዓመት የትጥቅ ትግል በተወሰኑ ሰዎች ተጠልፎ ለግል ስልጣንና ጥቅም ሲውል እኛ ዝም ብለን ተመልካች እንድንሆን ነው የሚጠበቀው? ወይስ የራሳችን ሚና መጫወት ይኖርብናል!?

ስምንት

የኢህኣዴግ መንግስትን የተቃወመ ሰው ወይ የፖለቲካ ድርጅት የትግራይ ህዝብ ጠላት እንደሆነ ኣድርገው በማቅረብ የትግራይን ህዝብ ለማጭበርበር የሚሞክሩ የመንግስት ኣካላት እንዳሉም ይታወቃል። ግን ህወሓትን መጥላት የትግራይ ህዝብን መጥላት ኣያሰኝም። ህወሓትን መቃወም የትግራይ ህዝብን መቃወም ማለት ኣይደለም። ምክንያቶች
(1) ህወሓት (ገዢው መደብ)ና የትግራይ ህዝብ (ተገዢው ህዝብ) አንድ አይደሉም፤ ሊሆኑም ኣይችሉም። ፓርቲና ህዝብ አንድ ተደርጎ የሚወሰደው ለፕሮፓጋንዳ (የህዝብ ግንኙነት) ሥራ ነው። የትግራይ ህዝብ ከህወሓት በፊት ነበር፤ ከህወሓት በኋላም ይኖራል።
(2) ተቃዋሚን በጠላትነት ማየት የፖለቲካዊ ኣስተሳሰብ ችግር ውጤት ነው። መቃወም ተፎካካሪ (ኣማራጭ ሃይል) መሆን እንጂ ጠላትነት ኣይደለም። ዴሞክራሲ ኣሰፍናለሁ የሚል መንግስት ተቃዋሚዎችን በጠላትነት መፈረጅ ተገቢ ኣይደለም።
(3) ሰዎች ወይ ድርጅቶች ህወሓትን (እንደገዢ ፓርቲ) የመቃወም ተፈጥሮኣዊ መብት ኣላቸው። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ከፈለገ (በፍላጎቱ ) ይምረጠውና ትግራይን ያስተዳድር (መብቱ ነው)። ህወሓት ላልመረጠው ህዝብ ኣሻንጉሊቶችን በመፈብረክ ሌሎች ህዝቦችን በእጃዙር የመግዛት መብት ግን የለውም።
ህወሓት ለኢትዮዽያ ህዝቦች መሪዎች የመምረጥ መብት ማን ሰጠው? ራሳቸው እንዲመርጡ ለምን ኣይፈቀድላቸውም? ስለዚ ህወሓትን ለመቃወም በቂ ምክንያት ኣላቸው። ይህን ሁኔታ በመቃወማቸው ‘የትግራይ ህዝብ ጠላቶች’ ሊያሰኛቸው ኣይችልም። የኢትዮዽያ ህዝቦች የራሳቸውን ተወካዮች በነፃነት የመምረጥ ሙሉ መብት ኣላቸውና።
(4) ህወሓት ለትግራይ ህዝብ የቆመ ድርጅት ከሆነ ለምን እንድንደራጅ ኣይፈቅድልንም? መደራጀትኮ ሃይል ይፈጥራል። ለምንድነው ተደራጅተን ሃይል እንዳንፈጥር የሚያደርገን? ከዚህ በላይ ጠላትነት ኣለ እንዴ? ስለዚ ‘የትግራይ ህዝብ ጠላት ህወሓት ነው’ ማለት እችላለሁ።
(5) የትግራይ ህዝብ (ባይሳካም) አንድ ኣስተሳሰብ እንዲኖረው ጥረት ማድረግ ትውልድን መግደል ነው። ብዙ ሰዎች አንድ ዓይነት ኣስተሳሰብ እንዲይዙ ለማድረግ የብዙዎቹ ኣስተሳሰብ መግደል ግድ ይላል። ኣስተሳሰብ ታፈነ፣ ተገደለ ማለት ደግሞ ትውልድን ተገደለ ማለት ነው። ምክንያቱም የለውጥ ምንጭ ኣስተሳሰብ ነው።
(6) ደሞ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አገዛዝ ነፃ መውጣት ኣይፈልግም ያለ ማነው? በትግራይ ሁሉም ቢሮዎች (ከላይ እስከ ታች) በተወሰኑ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ቁጥጥር ስር ነው። ማነው ትግራይ የነሱ ብቻ ናት ያለው? ትግራይኮ የሁላችን ናት? ወይስ የነሱ ባሮች (Slaves) ሁነን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል?
ማንም ሰው የመደገፍም የመቃወምም ተፈጥሮኣዊ መብት ኣለው። የመቃወም መብት የህወሓት የግል ስጦታ ኣይደለም። ህወሓት ሲፈልግ የሚሰጠን ሲፈልግ ደግሞ የሚከለክለን የግል ሃብቱ መሆን የለበትም።

ዘጠኝ

የስርዓቱ ተጠቃሚዎች (በቤተሰባዊ ሙስና) ገዢውን ፓርቲ በሚቃወሙ ግለሰዎች ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ከማካሄድ ኣይቦዝኑም። “የስርዓቱ ተጠቃሚዎች” ያልኩበት ምክንያት፡ ሕገ ወጥና ተቀባይነት የሌለው መንገድ በፈጠረው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥገኝነታቸው በራስ የመተማመን ስሜታቸው ካላሽመደመደው በቀር ሃሳባቸውን በነፃነት በሚፅፉ ሰዎች ስም የማጥፋት ዘመቻ ማድረግ ኣስፈላጊነቱ ኣይታየኝም ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው።
ህወሓቶች ለሚቃወማቸው ሰው ኣንድም ያስራሉ (ያዋክባሉ) ኣልያም ስም በማጥፋት ተግባር ይሰማራሉ። ለምን ስም ያጠፋሉ???
(1) በሙስና የበሰበሰ ስርዓት ተቃውሞ የሞትን ያህል ይፈራል። ምክንያቱም የግለ ሰዎች የተቃውሞ ፅሑፎች ድጋፍ ሊያሳጡት ይችላሉ። ድጋፍ ካጣ ስልጣን ሊለቅ ይችላል፤ ስልጣን ከለቀቀ የሰራውን ጥፋት ይጋለጣል።
(2) ጥቅሙ እንዲጎድልበት ኣይፈልግም (የእህል-ውሃ ጉዳይ ነው)። (“ኣብ ፃሕልና ኢድኩም ኣይትሕወሱ፤ ንሕና ክንበልዕ ንስኹም ጠጠው ኢልኩም ረኣዩ” ዝዓይነቱ።) ኣጥንት የያዘ ውሻ …… ይሆናል።
ህወሓት ተቃውሞ ሲያይልበት (ሁሉም ነገር ለብቻው ጠቅልሎ በመያዙ) ” እኔ ብቻ ኣይደለሁም የበላሁት፡ የትግራይ ህዝብም ኣብሮኝ በልቷል፤ ስለዚ እኔ ብቻ ተጠያቂ ኣልሁን፣ ከትግራይ ህዝብ ኣትነጥሉኝ” የሚል መልእክት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል።
የትግራይ ህዝብ ባልዋለበት (‘የማዩ የሰማዩ’) ሊያስወነጅለው እየሞከረ ነው (‘ጅብ ይበለሃል’ ከሚል ማስፈራርያ በተጨማሪ መሆኑ ነው)።
እኔ ግን እላለሁ፡ የህወሓት ሰዎች ባጠፉት ጥፋት የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ሊሆን ኣይገባም። እውነታውን መካድ የችግሩ መፍትሔ ኣይሆንም።

አስር

ሓሳብ በመግለፅ ብቻ ኣንድን ብሄር ወይ ፓርቲ ከስልጣን ለማውረድ ወይ ለማውጣት ኣይቻልም ። ሓሳባችን በነፃነት በመግለፃችን ከህወሓት ‘የባሱ’ ሃይሎች ስልጣን እንድይዙ ኣያስችልም ። እነዚህ ‘የትግራይ ጠላቶች ’ እየተባሉ የሚፈረጁ ግለሰዎች ተሳክቶላቸው ስልጣን ብይዙ እንኳ የራሳችውን ህዝብ ነው የሚያስተዳድሩ። ትግራይን የሚያስተዳዱርበት መንገድ የለም (እነሱም ትግራይን የማስተዳደር ስራ ‘ለኛ ይሰጠን’ ኣላሉም)። በህወሓት የሚሰጠን “እኔ ከሌለሁ ጅብ ይበላችኋል” ዓይነቱ ማስፈራርያ ግን ለትግራይ ህዝብ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው። ትግራይ የህወሓት ባለስልጣናት ብቻ ወልዳ የቀረች መኻን ኣይደለችም።
It is so!!!
ኣብርሃ ደስታ (ከመቐለ)
Paper taken from Aseged Tamene's blog, http://freedom4ethiopian.wordpress.com/

No comments:

Post a Comment

Who will Win: Fano or the Government?

  The government's war for "disarmament" in the Amhara region has become much more   complicated than everyone’s expectation. ...